Skip to main content

Posts

ስሜት እና እውነት

ስሜት የብረት ድስት ነው ፣ ሲጥዱት ቶሎ ይግላል ፣ ሲያወርዱት ቶሎ ይቀዘቅዛል፤ እውነት የሸክላ ድስት ነው ፣ ቶሎ አይግልም ፣ ቶሎ አይበርድም ። ስሜት የእንጀራ እናት ጡጦ ነው ፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የወተት ጋን ነው ። ስሜት ችግኝ ነው ፣ እውነት ግን የሚያስጠልል ዛፍ ነው ። ስሜት መጣሁ ብሎ የሚሄድ የመስከረም ዝናብ ነው ፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የነሐሴ ጠል ነው ። ስሜት የአሁን ንጉሥ ነው ፣ እውነት ግን ነገም የሚኖር ኃይል ነው ። ስሜት የርችት መብራት ነው ፣ እውነት ግን ግለቱ የሚጨምር የፀሐይ ብርሃን ነው ። ስሜት ቀን ነው ፣ ማታ ለመሆን ይቸኩላል ፤ እውነት ሌሊት ነው ፣ ወደ ቀን ይጓዛል ። ስሜት ሁሉን የሚያረክስ ነው ፣ እውነት ሁሉን የሚቀድስ ነው ። ስሜት ሮጦ የሚደክም ነው ፣ እውነት እያዘገመ የሚደርስ ነው ። ስሜት ተሳዳቢ ነው ፣ እውነት ግን አሸናፊ ነው ። ስሜት እገሌ የሚል ጠቋሚ ነው ፣ እውነት ግን እኔ የሚል ተነሣሒ ነው ። ስሜት ሰጥቶ የሚቆጭ ነው ፣ እውነት ግን ሰጥቶ የሚደሰት ነው ። ስሜት የእኔ ቃል የእግዜር ቃል የሚል ነው ፣ እውነት ግን የእግዚአብሔርን የሚያስቀድም ነው ። ስሜት ግልብ ነው ፣ እውነት ግን እውቀትን ያደላደለ ነው ። ስሜት ቢሞትም ሰማዕት አያሰኝም ፣ እውነት ግን የጽድቅ አክሊል አላት ። ስሜት ኢየሱስ ጌታ ነው እያለ በሥራው ያዋርደዋል ፣ እውነት ግን ክርስቶስን በሕይወቱ ያከብረዋል ። ስሜት በሬ ይነዳል ፣ እውነት ግን ራሱን ይሰጣል ። ስሜት ግሎ ያጋግላል ፣ እውነት ግን ሰምቶ ይጋግራል ። ስሜት የቅጠል እሳት ነው ፣ አያበስልም ኋላም አመድ የለውም ፤ እውነት ግን የሚያበስል ቀጥሎም የሚያሞቅ ፍም ያለው ነው ። ስሜት ጊዜያዊ እብደት ነው ፣ እውነት ግን መጥኖ መኖር ነው ። ስሜት ተናግሮ የሚያስብ ነው...
Recent posts

አፄ ምኒልክ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደ እኤአ ከ1889 እስከ 1913 ዓ. ም የገዙ #ኢትዮጵያዊ_ንጉስ ነበሩ። ኢትዮጵያ ከመሩ ከታላላቅ መሪዎች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ በስልጣን ዘመናቸው አገሪቷን በማዘመን እና በማጠናከር ዋና ተጠቃሽም ናቸው። ምኒልክ እኤአ በ1844 ዓ.ም አንኮበር በተባለ ቦታ ተወለዱ። እኤአ በ1889 ተቀናቃኛቸውን አፄ ዮሃንስ አራተኛን በጦርነት አሸንፈው ንጉሠ ነገሥት ሆኑ። ምኒልክ በስልጣናቸው ዘመን ኢትዮጵያን ለማዘመንና ግዛቷን ለማስፋት ሠርተዋል።  በርካታ ማሻሻያዎችን አድርገዋል ፥ አዲስ ነገርም አስተዋውቀዋል። ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ ባንክ ማቋቋም፣ የፖስታ ሥርዓት፣ እና ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት ጨምሮ።  በተጨማሪም ወታደራዊ ኃይሉን በማዘመን አዳዲስ የጦር መሣሪያዎችን በማግኘት ኢትዮጵያ እኤአ በ1896 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት የጣሊያንን ወረራ እንድታሸንፍ አድርገዋል። አጼ ምኒልክ የተካኑ ዲፕሎማት ነበሩ። ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ ከበርካታ የአውሮፓ ኃያላን መንግስታት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀመሩ። እኤአ በ1889 የውጫሌ ውል ከጣሊያን ጋር ተፈራረሙ። ይህም ውል ጣሊያን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ አንቀጽ ያካተተ ሲሆን ምኒልክ ይህን ውል አልቀበልም ብለው ውድቅ አድርገው ወደ አድዋ ጦርነት እንዲመሩ ፥ ክተት ጀማ እንዲሉ ሆኑ። አምኒልክ የሃይማኖት ነፃነትን በመቻቻል እና በመደገፍ ይታወቃሉ።  በኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች አብረው እንዲኖሩ ከማድረጋቸው በላይ በአዲስ አበባ መስጊድ እንዲገነባ ድጋፍ አድርገዋል።  የትምህርት ቤቶችን ግንባታና የሀገሪቱን የመሰረተ ልማት ግንባታ አበረታተዋል። በአጠቃላይ የአጼ ምኒልክ የንግስና ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የለውጥ ሂደት ነበር፤ አሁን...

ʺጃንተከል ዋርካው ሥር እትብቴ ተቀብሮ / ልቤ ጎንደር ይላል የትም የትም ዞሮ"

 ኀያላን ነገሥታት ዙፋናቸውን አስቀምጠውበታል፣ በሕዝብ ተከበው፣ በጠንካራ ጦረኞች ታጅበው፣ መኳንንቱን በግራና በቀኝ አሰልፈው ተቀምጠውበታል፣ የተስማማውን፣ እውነት የኾነውን ፍርድ ፈርደውበታል፣ ሀገር የሚያጸና፣ ሕዝብ የሚያኮራ ምክር መክረውበታል፣ ሊቃውንቱ ተሰባስበውበታል፣ ምስጢር እያመሴጠሩ እውነትን አውጥተውበታል፣ ጥበብን ገልጠውበታል፡፡ ጃን ተከል ዛፍ ብቻ አይደለም አዕዋፋት የሚኖሩበት፣ በማለዳና በምሽት የሚዘምሩበት፣ ጃንተከል ጥላ ብቻ አይደለም የደከማቸው የሚያርፉበት፣ ላባቸውን የሚጠርጉበት፣ ጃንተከል ዛፍ ብቻ አይደለም በተመቸ ጊዜ የሚቆርጡት፣ ከሥሩ ነቅለው የሚጥሉት፡፡ ጃንተከል ታሪክ ነው ነገሥታቱ ዙፋናቸውን አስቀምጠው በክብር የታዩበት፣ ጃንተከል የታላቅነት መገለጫ ነው ታላላቆቹ ታላቅ ነገርን ያስተማሩበት፣ ጃንተከል የፍትሕ ማረፊያ ነው መልካሙ ፍርድ የተፈረደበት፣ ጃንተከል የሊቃውንት መዳረሻ ነው፣ ጥበብ እንደ ዥረት የፈሰሰበት፣ ጃንተከል የጥበብ መገኛ ነው አበው በጥበብ ምስጢር ያሜሰጠሩበት፡፡ ጃን ተከል ግርማ ነው የጦር አበጋዞች በግርማና በኩራት የታዩበት፣ ጃንተከል የአንድነት ጥላ ነው በአንድነት የተሰባሰቡበት፣ ጃንተከል የፍቅርና የስልጣኔ መገለጫ ነው የሀገር ጥያቄዎች በውይይት የተፈቱበት፡፡ ነገሥታቱ በታላቁ ቤተ መንግሥት በክብር እና በአጀብ ይወጣሉ፣ በእልልታና በአጀብም ይከበባሉ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት በግርማ ይታያሉ፣ ሕዝቡም በእልልታና በሞገስ ያጅባቸዋል፣ ይከባቸዋል፣ ያከብራቸዋል፣ መልካሙን ምኞት ይመኝላቸዋል፣ ሺህ ዓመት ንገሡ ይላቸዋል፡፡ ጃንተከል ሕዝብና ንጉሥ፣ መኳንንትና መሳፍንት፣ ሊቃውንት፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ አዝማሪዎች፣ ነጋዴዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት፣ ፍትሕና ፍርድ የሚያዩበት ታላቅ ሥፍራ ነ...

ጥምቀትን በጎንደር፤ የጉዞ ማስታወሻ!

  ጥምቀትን በጎንደር፤ የጉዞ ማስታወሻ! ክፍል ፩ የ657 ኪሎ ሜትር የሙሉ ቀን ጉዞ ነው ከአዲስ አበባ - ጎንደር (በሞጣ በኩል)! ጥምቀትን አርባ አራቱ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቸው በድምቀት ወጥተው የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ-ጥምቀት የሚዘክሩበት ልዩ ትዕይንት ሲሆን፤ እኛም ተጠምቀን የልጅነት ክብርን ለመጎናጸፍ እንድንችል ልዩ-የሆነ ጥምቀተ ባህር በታላቁ ንጉሥ አፄ ፋሲለደስ አምሮ የተሰራልን በመሆኑ በዓሉን በአካል ተገኝቶ ለማክበር እጅግ ተመራጭ ነው፤ ጎንደር። ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ በአካል ለተገለጠላቸው ሁሉ የክርስቶስን ልዩ ልጅነት በመንፈስ ቅዱስ ርግብ አምሳልነትና በእግዚአብሔር ድምጽ በመሰላል የገለጡበት ተአምራዊ ክስተትን ነው በዓለ-ጥምቀት የሚያውጀው። ከሰማይ አብ፣ ከመኻል መንፈስ ቅዱስና በምድርም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ አጥማቂነት በባህረ ዮርዳኖስ ለሰው ልጅ ተገልጠው የሃይማኖት ሥርአት ይህ ነው ብለው አወጁልን። በዚህ ልክ ስላሶች ተገልጠው የሰውን ልጅ የወደዱበትን ጥግ አሳዬን፤ ለሰው ልጅ ምሳሌነትም ሰሩ፤ እንዲህ በማድረጋቸውም የሰው ዘር ሁሉ ሊጠመቅ እንደሚገባ ስርአት አኖሩ፤ እኛም ልንከውነው የሚገባንን አመለከቱን። እናም ጥምቀት ልዩ በዓል ነው፤ ሰማይና ምድር የተሳሰሩበት። አዎን ሰማያዊዉ ምድራዊ፤ ምድራዊዉም ሰማያዊ ሊሆን ይችል ዘንድ ሥርአት የቆመበት። ፍስሐ ወሰላም። ክከአዲስ አበባ ከሌቱ 11 ሰአት ተነስተን እየገሰገስን እግረ-መንገዳችንን(በመኪና ጎማም ቢሆን!) አንዴ በቀኝ መስኮት ሌላ ጊዜ በጋሻ በኩል አይናችን ይወረወራል። በመስኮት አሻግሬ በማየውና በምመለከተው ነገር ሁሉ እምዬ ኢትዮጵያ የሚሏት የበረከት፣ የልምላሜና የተአምራት ሀገር ታስደምመኝ ይዛለች። የሰላሌን መንገድ በጠዋት ላ...