ጥምቀትን በጎንደር፤ የጉዞ ማስታወሻ!
ክፍል ፩
የ657 ኪሎ ሜትር የሙሉ ቀን ጉዞ ነው ከአዲስ አበባ - ጎንደር (በሞጣ በኩል)!
ጥምቀትን አርባ አራቱ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቸው በድምቀት ወጥተው የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ-ጥምቀት የሚዘክሩበት ልዩ ትዕይንት ሲሆን፤ እኛም ተጠምቀን የልጅነት ክብርን ለመጎናጸፍ እንድንችል ልዩ-የሆነ ጥምቀተ ባህር በታላቁ ንጉሥ አፄ ፋሲለደስ አምሮ የተሰራልን በመሆኑ በዓሉን በአካል ተገኝቶ ለማክበር እጅግ ተመራጭ ነው፤ ጎንደር።
ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ በአካል ለተገለጠላቸው ሁሉ የክርስቶስን ልዩ ልጅነት በመንፈስ ቅዱስ ርግብ አምሳልነትና በእግዚአብሔር ድምጽ በመሰላል የገለጡበት ተአምራዊ ክስተትን ነው በዓለ-ጥምቀት የሚያውጀው።
ከሰማይ አብ፣ ከመኻል መንፈስ ቅዱስና በምድርም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ አጥማቂነት በባህረ ዮርዳኖስ ለሰው ልጅ ተገልጠው የሃይማኖት ሥርአት ይህ ነው ብለው አወጁልን።
በዚህ ልክ ስላሶች ተገልጠው የሰውን ልጅ የወደዱበትን ጥግ አሳዬን፤ ለሰው ልጅ ምሳሌነትም ሰሩ፤ እንዲህ በማድረጋቸውም የሰው ዘር ሁሉ ሊጠመቅ እንደሚገባ ስርአት አኖሩ፤ እኛም ልንከውነው የሚገባንን አመለከቱን።
እናም ጥምቀት ልዩ በዓል ነው፤ ሰማይና ምድር የተሳሰሩበት። አዎን ሰማያዊዉ ምድራዊ፤ ምድራዊዉም ሰማያዊ ሊሆን ይችል ዘንድ ሥርአት የቆመበት። ፍስሐ ወሰላም።
ክከአዲስ አበባ ከሌቱ 11 ሰአት ተነስተን እየገሰገስን እግረ-መንገዳችንን(በመኪና ጎማም ቢሆን!) አንዴ በቀኝ መስኮት ሌላ ጊዜ በጋሻ በኩል አይናችን ይወረወራል።
በመስኮት አሻግሬ በማየውና በምመለከተው ነገር ሁሉ እምዬ ኢትዮጵያ የሚሏት የበረከት፣ የልምላሜና የተአምራት ሀገር ታስደምመኝ ይዛለች።
የሰላሌን መንገድ በጠዋት ላፍ አድርገን የአባይን ሽለቆ ማየት ስንጀምር ግን ልቤ መሸፈት ጀመረ!
አእምሮዬ በሀሳብ ሠረገላ ተጭኖ አሁጉረ አፍሪቃን በሰሜን በኩል አቋርጦ፣ ግብፅን ረግጦ(ይበለው!) በሜዲትራንያን በኩል አውሮፓን ተሻገሮ፤ እልፍ ብሎም አትላንቲክ ውቅያኖስን ተራምዶ በአህጉረ አሜሪካ የሚገኘውንና ታላቁ ስምጥ ሸለቆ (Grand Canyon) ላይ አርፎ አሜሪካውያን የእኛን መሰል ድንቅ ምድራቸውን ለቱሪስት መዳረሻነት እንዲያገለግል ምን ያህል ተግተው እንደሰሩበትና እንደሚገለገሉበት በቅናት መንፈስ በአይነ-ህሊና አስተዋልኩት።
ይህ ጎሃ-ጽዮንን እልፍ እንዳልን ገዝፎ የሚታዬው የአባይ ሸለቆ ሳቢ ምድር ምን ያህል ለቱሪስት መዳረሻነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገቢ ማሳደጊያና ለመንፈስ ማደሻነት ሊውል ሲችል እስካሁን በድንግልና እንደሚገኝ ሳስብ ሀዘን ፊቴን ወረረው።
አእምሮዬ የባጥ የቆጡን እያነሳ ሲጥል አይኔ ግን የመንገዱን ግራና ቀኝ ያማትራል። በየትም ስንሄድ መንገድን አጅበው የተቀሰሩት የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ቋሚ እንጨቶች ከሸገር ጀምረው አሁንም አብረውን አሉ።
የአባይን ሸለቆ ወጥተን ወደ ደጀን ከተማ መግቢያ ስንቃና የጎጃም መልካ ምድር መመልከት ጀመርን። ወቅቱ እህሉ ታጭዶና ተሰብስቦ ተስፋ የሚሰጥና የሚያስደስት ክምር ሰርቷል።
የክምሮች መኖር ደስታ ከእርሻ ወደ ቤት ጓዳ መቅረቡን አመላካች ነው። ክምር ከተሰራ በኋላ የከብቶች አዛባ ለማገዶ ለሚውለው ኩበት መስሪያነት ብቻ አይውልም፤ ለአውድማ መለቅለቂያ፤ ለቤት ግድግዳ ማሰማመሪያና እንዲሁም ለጎተራ ማጠባበቂያ ይውላል።
አዝመራ ወደ ጎተራ ሲገባ የአመት ልፋትና ድካም ሁሉ መቋጫ አገኘ ማለት ነው። ጎተራው ሲጠግብ፣ ሸርፋው ሲሞላና ከብቶቹም እምቧ ሲሉ የደስታ መንፈስም ምድሪቱን ይሞላል። ወርሃ-ጥር እኮ የድግስና የጭፈራ ወር ነው።
በጥር ወር የሚከወነው ጥምቀት በዓል ከበአላት ሁሉ የሚለዬው ቤታችንም በሰብል ምርት የተትረፈረፈበት መሆኑም ይመስለኛል።
ግሬራዎች ወተት ሞልተው፤ ለጋ ቅቤ ይጠመቅባቸዋል፤ ቅቤው ተዝቆለት የሚቀረው ወተት አጓትና አይብ ይትረፈረፈዋል።
እውነትም ሰውም፣ ተፈጥሮም ፈጣሪም የሚከብሩበት ጊዜ ነው፤ ወርሃ-ጥር።
ጥምቀትን ተከትሎ ወርሐ ጥር ላጤዎች፣ ፍቅረኞችና የተጫጩ ሰዎች ለፍጹም አንድነት የሚዘለሉበት የፍስሐ ድንኳን ነው።
አሁን ውቢቷ ባህርዳር ደርሰናል፤ ጎንደር ከእንግዲህ ቅርብ ነው።
ደስ ብሎኛል፤ ደስ ይበላችሁ!
የነገ-ሰው ይበለን!

Comments
Post a Comment